የመንግሥት ባለሥልጣናት የሚጠቀሙባቸው ተሽከርካሪዎች ከአገር ውስጥ እንዲገዙ መመርያ ወጣ

በዳዊት እንደሻው

የሚኒስትሮች ምክር ቤት በቅርቡ ባወጣው መመርያ፣ የመንግሥት ባለሥልጣናት የሚጠቀሙባቸው ተሽከርካሪዎች ከአገር ውስጥ አምራችና ገጣጣሚዎች ብቻ እንዲገዙ አዘዘ፡፡

ምክር ቤቱ ከሐምሌ 28 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ ተፈጻሚ እንዲሆን ያወጣው መመርያ፣ የፌዴራል ባለ በጀት መሥሪያ ቤቶች ከፍተኛ ባለሥልጣናትና ሌሎች ተቋማት ኃላፊዎችን ይመለከታል፡፡ የተሽከርካሪ አጠቃቀም ወጪ ቆጣቢ፣ የሚመደቡ ተሽከርካሪዎችም ደረጃ ሲኖራቸው አመዳደቡም ፍትሐዊ እንዲሆን ለማድረግ ሲባል የወጣ መመርያ ነው ተብሏል፡፡

ሚኒስትሮች፣ ሚኒስትር ዴኤታዎች፣ የሕዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች አፈ ጉባዔዎችና ምክትል አፈ ጉባዔዎች፣ የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ፕሬዚዳንቶችና ምክትል ፕሬዚዳንቶች፣ ኮሚሽነሮች፣ ምክትል ኮሚሽነሮች፣ ዋናና ምክትል ዳይሬክተሮች፣ እንዲሁም የተለያዩ የተቋማት ኃላፊዎች የሚጠቀሙባቸውን ተሽከርካሪዎች ያካትታል፡፡

እስከ ዛሬ የመንግሥት ባለሥልጣናት የሚጠቀሙባቸው እንደ ቪኤይት፣ ጂናይን ፓጄሮና ፕራዶ ያሉ ውድና ወጪያቸው ከፍ ያሉ ተሽከርካሪዎች ለመስክ ሥራ ብቻ እንዲውሉ መመርያው ያዛል፡፡

ባለሥልጣናቱ በከተማ ማለትም በአዲስ አበባ ከተማ ለሚያደርጓቸው እንቅስቃሴዎች አነስተኛ ተሽከርካሪዎች ብቻ እንዲጠቀሙ ይገደዳሉ፡፡

እነዚህ አነስተኛ ተሽከርካሪዎች ወጪ ቆጣቢ፣ ውጤታማ ሆነው ቀጣይነት ያለው የሰርቪስ አገልግሎት ማግኘት እንዲችሉ አገር ውስጥ ከሚገጣጠሙ ድርጅቶች እንዲገዙ መመርያው ያዛል፡፡

በፌዴራል መንግሥት ተቋማት ሥር ያሉ ማናቸውም ጥቅም ላይ የሚውሉ ተሽከርካሪዎች፣ እንደማንኛውም የመንግሥት ተሽከርካሪ ለተፈቀደው ሥራ ብቻ ጥቅም ላይ እንዲውሉ ይደረጋል፡፡

እንዲሁም መሥሪያ ቤቶቹ ከተመደቡላቸው ተሽከርካሪዎች በላይ ሲያስፈልጋቸው፣ የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር የሥራቸውን ጠባይና ስፋት አገናዝቦ ጉድለት ለታየባቸው ተቋማት ተጨማሪ ተሽከርካሪዎች ይመደባሉ፡፡

የነዳጅ አጠቃቀምን አስመልክቶ የመንግሥት ባለሥልጣናት ለከተማ ሥራ ለሚገለገሉበት ለአንድ አውቶሞቢል በወር 135 ሊትር ቤንዚን ይፈቀድላቸዋል፡፡

ለመመርያው ተፈጻሚነት የየተቋሙ አመራሮች ኃላፊነት አለባቸው፡፡ የተሽከርካሪ አጠቃቀሙ በመመርያው መሠረት ተግባራዊ መደረጉን ተጠሪ ለሆኑበት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና ለገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር የአፈጻጸም ሪፖርት እንዲያቀርቡ በመመርያው ተገልጿል፡፡

ይህ መመርያ በተሽከርካሪ አስመጪዎች ላይ ምን ዓይነት ተፅዕኖ ሊፈጥር ይችላል በማለት ሪፖርተር ለኒያላ ሞተርስ ኩባንያ አንድ ኃላፊ ጥያቄ አቅርቦ ነበር፡፡ ኃላፊው ኩባንያውም ሆነ የተሽከርካሪ አስመጪዎች ማኅበር መመርያውን እንዳላዩት ገልጸው፣ ነገር ግን መመርያው በቀጥታ ተፅዕኖ እንደሚፈጥር ተናግረዋል፡፡ ለጊዜው ከዚህ በላይ ማለት እንደማይችሉም አክለዋል፡፡

Source: Ethiopian Reporter

Give a Comment